የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ኢዜአ ከተማዋን በአለማቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራረሙ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የባለብዙ ሃብት ባለቤት የሆነችውን ከተማ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስምምነት ነው ዛሬ የተፈራረሙት።

ስምምነቱን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተፈራርመዋል።

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ስምምነቱ ከተማዋን ለዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ከኢዜአ ጋር በጋራ መሥራቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም ሐዋሳ እንደ ከተማ ለአገሪቷ የብልጽግና ጉዞ አጋዥ የሆኑና የተሻለ ገቢ የምታገኝባቸውን ፕሮጀክቶች በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱንም ነው ከንቲባው የገለፁት።

ከኢዜአ ጋር በትብብር ለመሥራት የተደረሰው ስምምነትም የከተማዋን የቱሪዝም ሃብት፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት ክንውኖችን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑንም ከንቲባ ፀጋዬ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ አሉ ከንቲባው ሐዋሳ ያላትን እምቅ ሃብት በማስተዋወቅ እድገቷ እንዲፋጠንና የሚዲያው ሚና የማይተካ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ከሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር የተደረገው ስምምነት ለውጤታማ ሥራዎችና የጋራ ፍላጎቶች ስኬት መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሰኔ 9/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post