ሐዋሳን ዘመናዊ እና ለኑሮ ተስማሚ ከተማ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ከንቲባ ገለፁ

ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ይህን ያሉት ዛሬ በከተማዋ ከተሽከርካሪ ነፃ በሆኑ መንገዶች በተደረገው የብስክሌት እና የእግር ጉዞ ላይ ነው።

በሳምንት አንድ ቀን ይህ ከተሽከርካሪ ነፃ የእግር እና የብስክሌት እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ጤናውን እንዲያመርት ከማድረግ አንፃር ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም ነው ከንቲባው የገለፁት።

ከተማዋን ብለው ለጉብኝት የሚመጡ እንግዶች ከማንኛውም የትራፊክ መጨናነቅ ነፃ ሆነው መንቀሳቀስ እንዲችሉም ታሳቢ በማድረግ ስለመከናወኑም ነው ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ የገለፁት።

ተግባሩ ቀደም ሲል ከተማዋ ትታወቅበት የነበረውን የብስክሌት ትራንስፖርትን ለማበረታታት ነው ሲሉም ነው ከንቲባው የገለፁት።

በዚህ ረገድ አሉ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ ይህ አይነቱ ጥረት ሀዋሳን ዘመናዊ እና ለኑሮ ምቹ ከተማ ለማድረግ እየተወሰደ ካለው እርምጃ አንዱ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

አቶ ካሱ አሩሳ የሐዋሳ ከተማ ብልፅግና ጽ/ቤት ሀላፊ በበኩላቸው በከተማዋ የሚደረገው ከተሽከርካሪ ነፃ እንቅስቃሴ በዋናነት ህብረተሰቡ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እራሱን እንዲከላከል ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

ተግባሩ እንደ ሀገር አንዱ ስትራቴጂ ሆኖ ተግባራዊ ስለመደረጉ የገለፁት አቶ ካሱ ይህም በዋናነት በተለይም ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ አካባቢን በመፍጠር ለህብረተሰቡ ጤና ምቹ ሁኔታን እውን ማድረግ ነው ብለዋል።

ከተማዋ በተለይም በእረፍት ቀናት በርካታ የሀገርውስጥ እና የውጭ እንግዶች የሚገኙባት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አጋጣሚው የትራፊክ መጨናነቅን እና አደጋን ከመቀነስ አንፃርም ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል አቶ ካሱ።

በቀጣይ እንደ ከተማ በእነዚህ ቀናት በተለይም በመንገድ ዳር የከተማዋን ባህላዊ እሴት የሚያሳዩ እና የተለያዩ ሙዚቃዊ ትዕንቶችን ታሳቢ በማድረግ እና የንባብ ባህልን በሚያጎለበት መልኩ ህዝረተሰቡ በእግሩ እንቅስቃሴ ከማድረግ ባሻገር እየተዝናና ቀኑን በመናፈቅ ተሳትፎ ማድረግ የሚያስችል እቅድ እንዳለም ነው አቶ ካሱ የተናገሩት።

የሐዋሳ ከተማ ትራንስፖርትና የመንገድ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ አዳነ አየለ በበኩላቸው ይህ በሳምንት አንድ ቀን በከተማዋ የሚደረግ ከተሽከርካሪ ነፃ እንቅስቃሴ የእግር ጉዞን ከማበረታታት ባሻገር ወጪ ቆጣቢ አሰራርን የነደፈ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተግባሩ በቀጣይም ሌሎች የህብረተሰቡን ጤና የሚያጎለብቱ አሰራሮችን ጨምሮ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ዘመናዊ በሚያደርግ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ነው አቶ አዳነ የተናገሩት።

በእለቱ በከተማዋ አምስት ኪሎ ሜትር የሸፈነ የብስክሌት ግልቢያ ውድድር የተደረገ ሲሆን ለአሸናፊዎቹም የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሰኔ12/2014ዓ.ም

ሐዋሳ

Share this Post