የሐዋሳ ከተማ አተዳደር ከንቲባ ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ሚሊኒየም ፓርክን መልሶ ለማልማትና ከውሀ ሙላትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በዘላቂነት ለመከላከል ተስቦ በባለሞያዎች የተሰራን የፕሮጀክት ጥናት ውጤት በጽ/ቤታቸው ግምገማ አካሂደዋል።
በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ተመስርቶ ሐዋሳን የማልማት እና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ከተማ አስተዳደሩ በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ረ/ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ አስተዳደሩ የሐዋሳ ሚሊኒየም ፓርክን መልሶ ማልማት የሚያስችል ስራ ለመስራት ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝም ጨምረው ገልፀዋል።
የሐዋሳ ሚሊኒየም ፓርክ የደን መልሶ ማልማትና የጥበቃ ስራ ፕሮጀክቱን ለማከናወን መታቀዱን አቶ በላይ ሀሜሶ የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽ/ቤት ኃላፊ ጠቁምዋል።
ፕሮጀክቱ በጂ.አይ.ዜድ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኒክ ድጋፍ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑንም ነው አቶ በላይ ያመላከቱት።
በ2012 ዓ.ም መጨረሻ እና 2013 ዓ.ም መግቢያ ፓርኩ ከጎርፍ እና ከሐዋሳ ሐይቅ በተነሳ የውሀ ሙላት አማካኝነት ባጋጠመው ችግር በውስጡ የያዘው የደን ሀብት ውድመት እንዳጋጠመው የገለፁት አቶ በላይ ሀሜሶ ከጂ.አይ.ዜድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እና በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኒክ ድጋፍ ደረጃውን የጠበቀ ስራ ለመስራት አስተዳደሩ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሰራ እንደሚገኝ በመድረኩ ገልፀዋል።
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የስምጥ ሸለቆ ጥናትና ምርምር ባዮ ፊዚካል ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ምህረት ዳናጓቶ(ዶር) ፓርኩን ለቀጣይ 30 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ከውሀ ሙሌት ችግር በዘላቂነት መከላከል የሚያስችል ጥልቀት ያለው የጥናት ስራ መሰራቱን ጠቁመው በጥናት ውጤቱ ላይ ውይይት መካሄዱ አስተዳደሩ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስን ከማገዝ ረገድ ወሳኝነት እንዳለውም ገልፀዋል።
አቶ ደበበ ዳፊርሶ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው የውሀ ጥበቃ ስራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው የሚሰሩ ስራዎችን ጥናት ላይ ተመስርቶ ማከናወን እንደሚገባ ጨምረው ገልፀዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ሰኔ/14/2014/ዓም
ሐዋሳ