በቱሎ ቀበሌ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ሶስት ኢንተርኘራይዞች የተደረገው ድጋፍ የሲዳማ ክልል ስራ ክህሎትና ኢንተርኘራይዝ ቢሮ ከሐዋሳ ከተማ ስራ አሰሪና ሰራተኞች መምሪያ ጋር በመቀናጀት የተደረገ ነው ።
በስፍራው ተገኝተው የድጋፍ ያደረጉት የሐዋሳ ከተማ ስራ አሰሪና ሰራተኞች መምሪያ ሀላፊ አቶ ታሪኩ ጥላሁን ኢንተርኘራይዞቹ በገጠማቸው የፓምኘ ችግር ምክንያት በሚፈለገው ልክ ማምረት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
በአትክልትና ፍራፍሬ ስራ የተደራጁ እነዚህ ድጋፍ የተደረገላቸው 3 ኢንተርኘራይዞች የድግሪና የድኘሎማ ምሩቃን መሆናቸውን የገለጹት ሀላፊው ድጋፉ የኪራይ ወጪያቸውን ያስቀረና ምርታማነታቸውን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር የተደረገው የፓምኘ ድጋፍ ለያንዳንዱ 29 ሺህ አምስት መቶ ወጪ የተደረገበት መሆኑንም አቶ ታሪኩ አስረድተዋል።
የሐዋሳ ከተማ ስራ አሰሪና ሰራተኞች መምሪያ ም/ ሀላፊና የስራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተረፈ ሁሜሳ በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ በ12ቱም ቀበሌያት በመስኖ ስራ መልማት የሚያስችል አቅም መኖሩን ተከትሎ 3 ኢንተርፕራይዞች የመጀመሪያ ተጠቃሚ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
አቶ ተረፈ አክለውም ይህ መሰል ድጋፍ በሌሎች ቀበሌያትም እንደሚቀጥል ገልጸው የመሸጫ ቦታና የገበያ ድጋፍም እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
ዛሬ የተደረገው ከሁሉ አቀፍ ድጋፍ አንዱ መሆኑንም ነው አቶ ተረፈ የገለጹት።
የሐዌላ ቱላ ክ/ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤቶ ሀላፊ አቶ ሻምበል ጎኔ በበኩላቸው ወጣቶች ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ተጠቅመው ምርታማነታቸውን በማሳደግና ውጤታማ በመሆን ትርፋቸውን በሌላ መስክ ለማሸጋገር አስቻይ ነው ብለዋል።
ወጣት መብራትና ገዛኸኝ ካሳ የተደረገው ድጋፍ የብዙ ግዜ ችግራቸውን የፈታ እንደሆነ ገልጸው ለፓምኘ ኪራይ በቀን 1 ሺህ ብር ወጪ እንዳስቀረላቸውም ገልጸዋል።
ወጣቶቹ አክለውም በዚሁ ስራ በስራቸው ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።