በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር በዘመናዊ የከተማ መሬት ምዝገባና መረጃ አያያዝ በ3 ወራት ውስጥ 5ሺህ ይዞታዎችን ማረጋገጥ የሚያስችል የመጀመሪያ ኘሮግራም ተካሄደ በመድረኩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ሚልክያስ ብትሬ በUIIDP የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፍያ ኘሮግራም የከተማ መሬት ይዞታን በሰነድና በልኬት ለማረጋገጥ የሚያስችል ኘሮግራም መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሚልክያስ ከተማዋ ቀድማ ስራውን የጀመረች በመሆኑ እስከ አሁን በነበረው 12,500 ይዞታዎችን ማረጋገጥ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በዚሁ ዓመት ብቻም ከተማ አስተዳደሩ 10 ሚሊየን ብር መድቦ 4000 ይዞታዎችን ማረጋገጥ የተቻለ መሆኑን የገለጹት አቶ ሚልክያስ በዚህም ሶስት ክ/ከተማዎችን በካዳስተር ስርዓት ማጠናቀቅ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ተጨማሪ 5ሺህ ይዞታዎችን ለማረጋገጥ ከአማካሪ ድርጅት ከትሮኘካል ጆኦስፓሻል ጋር ውል የተገባ መሆኑን ሀላፊው አክለዋል።

የከተማዋን የመሬት አያያዝ ስርዓት ማዘመን በዘርፉ የሚታየውን የመሬት መረጃ ማነቆ ለመፍታት፣ህገወጥነትን ለመከላከል፣ ከመሬት የሚገኝ ገቢን ከማሳደግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል።

ካዳስተር ባልተሰራባቸው ሶስት ክ/ከተማዎች በ5 ቀጠናዎች ውስጥ በሚገኙ 25 ሰፈሮች የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሐዋሳ ከተማ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ዩኒት ሀላፊ አቶ ስኖስ ሲንታሮ ስራው ሰነድ ያለውንና ሰነድ አልባ ይዞታን ከማረጋገጥም በላይ በርካታ ጠቄሜታ እንዳለው ገልጸው ህብረተሰቡም የበኩሉን ሊተባበር ይገባል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል የከተማ መሬት ይዞታ መብት ምዝገባ ዳይሮክተሬት የሆኑት አቶ አበበ ኩየራ ለስራው አስፈሊጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መህናቸውን ገልጸዋል።

የታቦር ክ/ከተማ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ፍቅሬ በበኩላቸው የመሬት ምዝገባውን ዘመናዊ ማድረጉ ለያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ ለመንግስት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ሰኔ 13/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post