የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደር ኘሮግራም ሐዋሳ በሀዌላ ቱላ ክ/ከተማ በፍንጫዋ ቀበሌ የ2.3 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

የተደረገው ድጋፍ ለእድር፣ ለገንዘብ ቁጠባና ብድር ማህበራት፣ ለእናቶች ሲሆን በገንዘብና በቁሳቁስም የሚገለጽ ነው።

የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደር ሐዋሳ የኘሮግራም ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ ደጀኔ እየተደረገ ያለው ድጋፍ የአካባቢውን ህብረተሰብ ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ገለጸዋል።

አቶ ጸጋዬ ማህበራቱ ተጠናክረወና እራሳቸውን በኢኮኖሚ አብቅተው ከተረጅነት ወጥተው ሌሎችን የሚደግፉና የሚያግዙ እንዲሆኑ ማስቻል የድርጅቱ ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጴጥሮስ ዩሐንስ የኤስ ኦ ኤስን መርህ በመውሰድ ዛሬ ድጋፍ የተደረገላችው ማህበራት በተለይም ህጻናትን የሚደግፉ ተቋማት መሆን እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

አቶ ጴጥሮስ አክለውም በሀገራችን ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመሻገር ለተሰለፍንበት ዓላማ አንድ ሆነንና ለታቀደው ዓላማ ብቻ በማዋል ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል።

የገንዘብ ቁጠባዎች ይበልጥ የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ በስልጠና፣ በቁሳቁስ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ጭምር እገዛ ለማድረግ አቶ ጴጥሮስ ቃል ገብተዋል።

አቶ ተክሉ አርጋዬ የኤስ ኦ ኤስ ህጻናት መንደር ኘሮግራም ሐዋሳ የኤቢሲዲ ኘሮጀክት ዋና አስተባባሪ ናቸው።

እንደ አቶ ተክሉ ገለጻ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 250 ሺህ ለቢሮ ማደራጃ፣ 7 መቶ ሺህ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ብድር፣ 195 ሺህ ብር ለእናቶች ስራ ማስጀመሪያ፣ ለ አንድ እድር ወፍጮ ተከላ የሚውል 280 ሺህ ብር፣ 250 ሺህ ብር ደግሞ በጣም ለተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጸዳጃ ቤት ግንባታ እና 250 ሺህ ብር በጣም የተጎዱ ቤቶች የሚጠገኑበት መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተክሉ አጠቃላይ የኘሮግራሙ አላማ ሲናገሩ ማህበራቱ ከሚያገኙት ትርፍ ችግርተኛ የሆኑ ልጆችን መደገፍና ኑሯቸውን አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ማስቻል ነው ብለዋል።

የኘሮግራሙ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ለህጻናት የት/ቁሳቁስ በመደገፍ፣ ት/ቤቶችንና መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም ሌሎች በርካታ እገዛ እያደረገ ያለውን የኤስ ኦ ኤስ መንደር ኘሮግራም ሐዋሳ በእጅጉ አመስግነዋል።

የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ

ታህሳስ 8/2014 ዓ/ም

ሐዋሳ

Share this Post